Tuesday, June 2, 2015

የሀላላ ካብ/STONE WALL OF KING HALALA IN DAWRO ZONE

የሀላላ ካብ/WALL OF HALALA

king halala wall
ብዙዎች ስለምን ይህን የመሰለ ቅርስ ሚስጥር ሆኖ ሳይወራለት ቀረ በሚል ይቆጫሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ቀኑ አልመሸም በሚል የኢትዮጵያውያን ድንቅ እሴት ማሳያ ነውና እንተርክለት ሲሉ ዝናውን ይናገሩለታል፡፡ የሁሉም ድምር ግን ከዳውሮዎች ምድር ያለው ድንቅ ቅርስ የኢትዮጵያውያንነታችን የኩራት ተምሳሌትነትን መዘከር ነው፡፡

የቻይናውን ግንብ የመሰለው ይህ ግንብ እንዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖሯል ቢባል ለሰሚው ግራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያዊ ሰሚ፡፡ ምክንያቱም ይህ ከአምስት መቶ ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረው ካብ አንድ ዙር ርዝመት 170 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝም ነው፡፡ በዚህ ርዝመቱ የጎፋ፣ የወላይታን፣ የወላይታን፣ የካፋንና የጅማን ድንበር በሙሉ ያካልላል፡፡

የድንጋዩ ካብ ስራ ከ1582 እስከ 1607 ባለው ጊዜ የተሰራ ሲሆን በተለይም በወላይታ በከምባታና በጎፋ ወሰን ያለው ግዙፍ እና ረዥሙ ካብ ከኤሌ እስከ ዛባ ጋራባ የተዘረጋው ነው፡፡ ይህ ግንብ ከሁለት ሜትር ተኩል እስከ ሶስት ሜትር የሚደርስ ቁመት ሲኖረው ከሁለት ሜትር ተኩል በላይ የጎን ስፋት አለው፡፡

የዳውሮ ብሄረሰብ የሚገኘው በደቡብ ክልል ነው፡፡ የዞኑ ማእከል ታርጫ ትባላለች፤ ታርጫ ከሐዋሳ 282 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ በጅማ ዳውሮ 479 እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወላይታ ሶዶ ታርጫ 455 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ዳውሮዎች በባህል እሴቶቻቸው የዳበሩ የበርካታ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የዳውሮዎች ታሪክ ለታላቋ ኢትዮጵያ አንድ የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ይህ ታሪክ አያሌ ድንቅ ታሪካዊ ቅርሶችን መፍጠር ችሏል፡፡

የዳውሮ ካውካ ስርወ መንግስት በዳውሮ የአስተዳደር ስረዓት የጎላ ታሪክ የሚይዝ ነው፡፡ ከዳውሮዎች የታሪክ ድርሳን ስማቸው ደምቆ የተጻፈው ንጉስ ሃላላ በኢትዮጵያ መሪዎች ታሪክ ለትውልድ ቅርስ ትተው ካለፍ የኩራት አብነቶች አንዱ ናቸው፡፡

ንጉስ ሃላላ ስልጣንን በግል ጠቅልሎ ከመያዝ ልማድ በመውጣት አያሌ አዳዲስ የአመራር ስልቶችን ማሳየት የቻሉ መሪ ነበሩ፡፡ በተለይም ስልጣንን ለህዝብ በማካፈልና በየደረጃው በማውረድ ህዝባዊ አገዛዝን መመስረቱ ላይ የተዋጣላቸው እንደሆኑ የህዝብ አንድነትን እንደሚጠይቁ የሚያሳዩት የታሪክ ቅርሶች ምስክሮች ናቸው፡፡  

ጦረኛነታቸውም ቢሆን ድል አድራጊነትን የተሞላ እንደነበር የሚነገርላቸው ንጉስ ሃላላ የዳውሮን ድንበር ከልሎ በማጠር አልፎም በማስከበር ስኬታማ የአስተዳደር ዘመን አስቆጥረዋል፡፡ ዛሬ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ ዙሪያ ተገትሮ ታሪክ የሚመሰክረው የንጉስ ሃላላ ካብ ለዚሁ የዳውሮን ቅጥር ለማስከበርና ለጠላት መከላከያነት የተከተረ ነው፡፡

የሀላላ ካብ ከካቡ ውጭ የሚመጣውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ለመከላከል እንዲያስችል ሰባት በሮች ተበጅተውለታል፡፡ በሮቹ የየራሳቸው መጠሪያ ስም እና መገለጫ አላቸው፡፡ እነዚህም በሮች በየኤላ የከፋ በር፣ የቁጫና የጎፋ በር፣ የዚማ ወላይታ በር፣ የዩሊማሎ በር፣ የዛባ ጋራዳ የቦምቤ በር፣ የአባ የጂማ በር ይባላሉ፡፡

ድንጋይ በድንጋይ ላይ በማነባበር ግዙፍ አለቶችን በታትኖ ይህንን መሰል አንዳች ያልተወራለት ረዥም ግንብ በመገንባት ለታሪክ ማኖር የቻሉት ቀደምት የዳውሮ ነገስታት ጥለውት ያለፍት ቅርስ ወደ ገንዘብ ሊቀየር ሊጎበኝና የውጪ ምንዛሪን ልናፍስበት የሚያስችል የቱሪዝም ሃብት ነው፡፡

በተለይም ቅርሱ በድንቁ ዲንኬ የሙዚቃ መሳሪያ እያጫወቱ እንግዳን ማስተናገድ በሚችሉት የዳውሮ ህዝቦች ማእከል መገኘቱ ጎብኚ የበለጠ በቆይታው እንዲደሰት የሚያደርግ ነው፡፡ እግረ መንገድ አስደናቂውን የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክንም ለመጎብኘት ምቹ ነው፡፡ ስለ ዳውሮ ተጀመረ እንጂ አልተወራም አያሌ የመስህብ ሃብቶችን የያዘ ድንቅ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ቀጠና ነው፡፡ 
 Edigetu-UoG-2007https://www.facebook.com/dawru.tube

1 comment:

  1. click here to get more news about Dawro https://www.facebook.com/dawru.tube

    ReplyDelete